Friday, June 13, 2014

’ውዥንብር’’ ምርጥ የማስታወቂያ መንገድ



‘’ውዥንብር’’ ምርጥ የማስታወቂያ መንገድ
      ከሰው ልጅ እጅግ ከሚያስደንቁ ተፈጥሮዎች መካከል ፈጠራ አንደኛው ነው ።  ሰው የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ፣ አላማውን ለማሳካት ፣ ኑሮውን ለማቅለል ብዙ ነገሮችን ይፈጥራል፣እየፈጠረም ነው ወደ ፊትም ይፈጥራል። ውዥንብር አንድ የማስታወቂያ መንገድ አድርጎ ማምጣት እጅግ የተዋጣለት የማስታወቂያ ፈጠራ ነው።

      ልጅ ሆኜ በግቢያችን ውስጥ (አንደኛ ደረጃ ት/ቤት) ታዋቂ ከሆኑ እንዲሁም ከማይረሱ ልጆች መካከል  ሰርካለም አንዷ ነች ። ሰርካለምን አሁን ድረስ የማስታውሳት ቆንጆ ሆና ፣ ጎነዝ ሆና ወይም የተለየ ነገር ኗሯት አይደለም እሷን ታዋቂ ያደረጋት በአጋጣሚ የተፈጠረ ውዥንብር ነው ፦ ሙሉ ስሟ ሰርካለም ጥላሁን ገሰሰ ነው ። ይህን ልብ ብሎ ያጤነው አንዱ ተማሪ የዘፋኙ ጥላሁን ገሰሰ ልጅ ነች ብሎ አስወራ ከዛን ቀን በኋላ ሁሉም ልጅ ትኩረት የሚሰጣት ልጅ ሆነች ። ጥላሁን ገሰሰን በቲቪ ስናይ የሰርካለም አባት እንል ነበር የሱ ልጅ አለመሆኗን ያወኩት ከረጅም ጊዜ በኋላ አባቷን የማየት እድል ካገኘው ወዲህ ነው እናም ውዥንብር እንደ ማስታወቂያ መጠቀም ለመታወቅ ትልቅ ሚና አለው።

    ድምጻዊ መሃመድ ተሾመ (ድንቢ) ቴዲ አፍሮን እኔ እበልጠዋለው የሚል አስተያየት ሰጠ ተባለ ይህ ከተባለ በኋላእራሱ አስተባበለ ነገር ግን በዚህ ወቅት የ ቴዲ አድናቂዎች ልጁ ላይ ብዙ ስድብ ሲያወርዱበት ቁም ነገሩ ያለው እዚህ ላይ ነው።በመጥፎም ሆነ በጥሩ መሃሙድ በብዙ ሰዎች ዘንድ ሆነ ሰዎችም ቴዲን እንዲህ ያለው እሱ ምን አይነት ዘፋኝ ቢሆን ነው ብለው የሱንም ዘፈኖች ሰሙ በዚህ ሰአት በግርግር መሃሙድ ታዋቂነትን አተረፈ ዘፋኝ መሆኑንም ለብዙዎች አስተዋወቀ።

       ውዥንብር ከማስተዋወቅ( ከማሳወቅ ) አንጻር ትልቅ ጥቅም ቢ ኖረውም ጉዳቱም ያንኑ ያህል ነው። እውቅናን ለማግኘት ተብለው የሚወሩ ወሬዎች ስራቸው ሰፍቶ ወደ አልታሰበ አቅጣጫ ሊያመሩ የሚችሉበትም አጋጣሚ ያንኑ ያህል ነው አንዳንድ ጊዜ አንድን ወሬ ተከትሎ የሚመጣው ነገር ባለጉዳዮቹን ወዳልታሰበ እና ችግር ውስጥ ሲከት ይታያል  

       ውዥንብር እንደማስታወቂያ ይጠቀሙታል ብዬ የማስበው በተለይ አርቲስቶችን ነው ። ዘፋኞች ወይም የፊልም እና የቲያትር ሰሪዎች እንዲታወቁ ከፈለጉ ውዥንብር ዋናው መንገዳቸው ይሆናል ። በ አንድ ወቅት ስሙን በውል የማላስታውሰው አሜሪካዊ ጸሀፊ ሞተ ተብሎ ተወራ ከ ጊዜያት በኋላ ‘’ አልሞትኩም እንዲሁም ለአድናቂዎቼ አዲስ ስራ ይዤ መጥቻለው ‘’ አለ በቃ የሱ መጽሀፍ ለጉድ ተቸበቸበ ። 

    ይህ ውዥንብር አመት ሙሉ ቢያስተዋውቅ ሊገኘው ከሚችለው በላይ በአንድ ወሬ ብዙ ነገርን አገኘ። ከውዥንብር በላይ ባለታሪኩ የሚሰጠው አስተያየት የውዥንብሩ ዋነኛ አካል ነው ። ብዙውን ጊዜ እንደምንታዘበው አንድ ታሪክ ከተፈጠረ በኋላ ባለቤቱ ልክ ነው ወይም አይደለም ብሎ ይናገራል በዚህ ግርግር ትልቅ ማስታወቂያ ይሰራል ።

      የ አለማችን ምርጥ አ እግር ኳስ ተጫዋቾች በእኔ ግምት ውዥንብር በሚገባ ይጠቀማሉ ። ሉበት ክለብ ካልተመቻው በ ወኪላቸው አማካኝነት  ሌላ ክለብ እንደጠየቃቸው ያስወራሉ ይህንን የሚሰሙት ሚድያዎች በ አካል ሲጠይቋቸው አላልኩም ብለው ያስተባብላሉ ። ስለ እነሱ በተደጋጋሚ በተወራ ቁጥር ሌሎች ክለቦች ፍላጎት ያሳድራሉ ጥያቄም ያቀርባሉ።ስለ ተጫዋቹ በተወራ ቁጥር ተፈላጊ ይሆናል።

        ከላይ እንደተገለጸው ውዥንብር ምንም ያህል እውቅናን ማምጣት ቢችልም በ መጥፎ በኩል የተገኘ ስም ግን ይጠቅማል የሚል እምነት የለኝም እንድ ሰው ለመታወቅ ብሎ የጦር መሳሪያ ያዘዋውራል የሚል ውዥንብር በራሱ ላይ ቢፈጥር በሰዎች እና በሚዲያ በደንብ ሊታወቅ ይችላል ቢሆንም ግን ከዛ በኋላ የተረጋጋ እና ሰላማዊ ኑሮ ሊኖር እይችልም ለዚህም ነው ውዥንብር ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳቱም ያንኑ ያህል ነው ። ታዲያ በውዥንብር መታወቅ ይሻላል ወይስ በሰራነው ሥራ ልክ ትክክለኛ ማስታወቂያ በመስራት መታወቅ ?  

 

No comments:

Post a Comment